አዲሱ የዩኒቨርሲቲያችን ፕሬዝዳንት ስራ ጀመሩ

Share this story

Posted on: Apr 18,2018

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቂና ብቁ የሰው ሃይል በማዘጋጀት የአገራችንን የመፈፀም አቅም በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመግባት የሚደረገውን ርብርብ ማቀላጠፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲያችን የትምህርት አደረጃጀት ባልተማከለ ሁኔታ ለጥራት፣ ተገቢነት፣ ተደራሽነትና ፍትሃዊነት ትኩረትና ምላሽ በሚሰጥ አግባብ እንዲፈፀም ያስቀምጣል፡፡

በተጨማሪም ትምህርት አሳታፊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ውጤታማና ብቁ አመራር እንዲኖረው ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በተመሳሳይ አገራዊው የማስፈፀም አቅም ስትራቴጂያችንንና ሌሎች የትምህርት ዘርፉ አዋጆችና ደንቦች በማስቀመጥ ተቋማትን ውጤታማ ማድረግ ይፈለጋል፡፡

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ተደራሽነት፣ ጥራት፣ ተገቢነትና ፍትሃዊነትን በማሻሸል፣ ችግር ፈቺ የሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በመስራት፣ ፍላጎትን ማዕከል ያደረጉ የማህበረሰብን አገልግሎቶችን በመስጠት፣ ተፎካካሪና ብቁ ትውልድን በማፍራት የሀገራችንን የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ውጤታማ የሚያደረግ መዋቅር፣ አመራርና አስተዳዳሪ ይፈልጋል፡ ይህንን ለማሳካት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር በ2010 የትምህርት ዘመን ሀገራችን ውስጥ በአሉት የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የኃላፊነት ጊዜያቸውን በጨረሱ የአመራር ቦታዎች ላይ ከፍተኛ ችሎታ ያለው፣ ብቁና ራሱን ለስራ የሰጠ ተወዳዳሪ አመራር ክፍተት ባለባቸው የስራ መደቦች ላይ አወዳድሮ ተገቢውን ሰው ማስቀመጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቀዳሚ ተግባራቸው እንደሆነ አስቀምጧል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አመራር ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአመራሮችን ምርጫ፣ ሹመት/ምደባ ለመደንገግ የወጣ መመሪያ 002/2009 መሠረት በማድረግ ለድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት፣ ም/ፕሬዝዳንቶችን እና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ለመመልመላና ምርጫ ለማካሄድ አምስት አባላት የአሉበት ኮሚቴ አቋቁሞ ስራው እንዲጀምር አድረጓል፡፡

ቦርድ እነዚህን የኮሚቴ አባላት በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ይሁንታ እንዲያገኝ ከአደረገ በኃላ የዩኒቨርሲቲው ሴኔትን የሚወከል፣ ከመምህራን ማህበር፣ አለም አቀፍና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የምልመላና ምርጫ ኮሚቴ እንዲሆኑ በአብላጫ ድምፅ ሴነቱ አጽድቆ ስራው እንድሰራ ተደርጓል፡፡

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ትምህርት ሚ/ር ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች ለምልመላና ምርጫ በተዘጋጀው የመመዘኛ መስፈርት መሰረት ኮሚቴው የተዘጋጁትን ዝርዝር መስፈርቶች ለዩኒቨርሲቲያችን የካወንስል አባላት ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ በዝርዝር መስፈርቶቹን ማስተቸት እና በኮሚቴው የምልመላና ምርጫ የአሰራር ደምብ ላይ ውይይት በማድረግ ጠቃሚ ግብአቶችን ማሰባሰብ ተችሏል፡፡

ከጥር 29/2010 ዓ.ም ጀምሮ ለፕሬዝዳንትነት በተወዳደሩ አመልካቾች ዙሪያ የዶክመንታቸውን ትክክለኛነት (Originality) እና እነዚህ ተወዳዳሪዎች በስራ ቦታቸው ያላቸው ትጋት፣ ኃላፊነትን መወጣት ብቃታቸው፣ ከሌላው የተቋሙ/የመስሪያ ቤቱ ማህበረሰብ ጋር ያላቸው ተቀባይነት፣ የተግባቦት ክህሎታቸው፣ የጊዜ አጠቃቀማቸው፣ በስራ ቦታቸው ያላቸው ዲስፕሊንና እና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ከስራ ባልደረባ፣ ከቅርብ ኃላፊና ከተቋሙ የበላይ ኃላፊ መረጃ የማሰባሰብና የማጠናከር ስራ ተሰርቷል፡፡

ዕጩ ተወዳዳሪዎች

 

 

 

 

 

 

የዩኒቨርሲቲያችን ቦርድ አመራር አባላት፣ የሴኒት አባላትና የካውንስል አባለት ዕጩ ተወዳዳሪዎችን በተለያየ መድረክ በመገምገም ውጤት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ የውጤት አሰጣጡ ሂደት የካቲት 23/2010 ዓ.ም የቦርድ አመራር አባላትና የሴኒት አባላት የዕጩዎችን ስትራቴጂክ ዕቅድ የገመገሙ ሲሆን የካቲት 24/2010 ዓ.ም የካውንስል አባላት የፓናል ቃለ-መጠይቅ የተሰጠውን ምላሽ በመገምገም ውጤት ሰጥተዋል፡፡ እያንዳንዱ የቦርድ አባል፣ የሴኔት አባል ከ25% እንዲሁም አስቀድሞ ውጤት የሰጡትን የሴኔት አባላትን ሳያካትት እያንዳንዱ የካውንስል አባል ከ20% ለስምንቱም ዕጩ ተወዳዳሪዎች የሰጠው ውጤት ተመዝግቦ የካውንስል እና የቦርድ አባላት በአሉበት ወዲያውኑ በስክሪን (LCD) በተደገፈ 45% ዉጤቱ ለሁሉም በሚታይ መልኩ ይፋ ተደርጓል፡፡

ከእዚያም የ45% ግልፅ የሆነ የውጤት አሰጣጥ ስነ-ስርዓት በመገምገም የቦርድ ሰብሳቢና አባላት እንዲሁም የካውንስል አባላት ኮሚቴው አመስግኖ መርሀ ግብሩን አጠናቋል፡፡

ኮሚቴው የዕጩ ተወዳዳሪዎችን ውጤት አስልቶ ከ100% ማስቀመጥ ችሏል፡፡ የካቲት 25/2010 ዓ.ም የኮሚቴው ሰብሳቢ አጠቃላይ የውጤት አሰጣጡን ሂደት ከገመገሙ በኋላ ለቦርድ የሚቀርቡትን 5 ዕጩ ተወዳዳሪዎችን እንደውጤት ተከተላቸው ለቦርድ አቅርቧል፡፡

የዩኒቨርሲቲያችን ቦርድ አመራር የምልመላና ምርጫ ኮሚቴ በአቀረበለት አምስት ዕጩዎች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ከአደረገ በኋላ ሦስት ዕጩዎችን መለየት ቸሏል፡፡

በመቀጠልም በመመሪያው መሰረት እነዚህን ዕጩዎች ለትምህርት ሚኒስቴር በማቅረብ የዩኒቨርሲቲውን በቀጣይ በፕሬዝዳንትነት የሚመራውን አንድ ዕጩ እንዲለይ በማድረግ አሹሟል፡፡ በእዚሁ መሰረት ውድደሩን በከፍተኛ ውጤት ሲመሩ የነበሩት ዶ/ር ያሬድ ማሞ ለቀጣይ ስድስት አመታት ዩኒቨርሲቲችንን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩ መሆናቸው ከትምህርት ሚኒስቴር በተፃፈ ደብዳቤ ይፋ ተደርጓል፡፡                                              የዩንቨርሲቲው የቦርድና የሴኔት አባላት

በተያያዘ ሁኔታ ዶ/ር ያሬድ ማሞ ስራቸውን በዩኒቨርሲቲያችን ከሚገኙ የተለያዩ አመራርና የሠራተኛ ተወካዮች ጋር በተለያየ መድረክ ትውውቅ በማድረግ ስራቸውን መጋቢት 24/2010 ዓ.ም በይፋ ጀምረዋል፡፡

ምርጫና ምርጫን ብቻ ተከትሎ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የአመራር መሾምና የአመራር ክፍተት መድፈን የተሻለ አሰራር እንደሆነ ይታመናል፡፡ ዩኒቨርሲቲያችንን ለመምራት የተሾሙት ፕሬዝዳንት የተቋሙን ርዕይ ከዳር ለማድረስና የተሰጠውን ተልዕኮውን ለማሳካት የተጀመረውን መልካም ስራ በማስቀጠል፣ የጎበጠውን በማቅናት፣ ሁሉንም የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ ለውጤት በማንቀሳቀስ ተቋሙን በብቃት እንዲሚመሩ በማመን (DDU Times) መልካሙን ሁሉ ትመኛለች፡፡

ዩኒቨርሲቲያችን 800,000 ብር የሚጠጋ መደበኛና ካፒታል በጀት የሚያንቀሳቅስ ሲሆን ተቋሙ በስሩ ከ10,760 ሺህ በላይ መደበኛ ተማሪዎችን በ39 የትምህርት ፕሮግራሞች ተቀብሎ እያስተማረ ሲሆን፣ ከ1,177 በላይ በስራና በትምህርት ላይ ያሉ መምህራን እንዲሁም ከ1517 ሺህ በላይ የአስተዳደር ሠራተኞችን የያዘ የመንግስት ከፍተኛ ተቋም ነው፡፡

ለለውጡ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና አጋር አካላት በሙሉ እንደ ከዚህ ቀደሙ ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ጋር በቅርበት በመስራት ለምናደርገው የልህቀት ግስጋሴ ስኬት ከፕሬዝዳንቱ ጎን እንድትቆሙ በአለም አቅፍና ህዝብ ግኑኝነት ዳይሬክቶሬት ስም ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በድጋሚ ዶ/ር ያሬድ ማሞ እንኳን ወደ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በሠላም መጡ በማለት የዝግጅት ክፍላችን ደስታውን ይገልፃል፡፡ ከእዚሁ ጋር አያይዘን ሁሉም የዩኒቨርሲቲያችን ማህበረሰብ አዲስ ተሹመው የመጡትን የዩኒቨርሲቲያችንን ፕሬዝዳንትን በቅን ልቦና፣ በቁርጠኝነትና በስራ ተነሳሽነት ስሜት ከጎናቸው በመሆን ለዩኒቨርሲቲያችን እድገትና ለውጥ በስራ እንዲያግዛቸው ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡