በህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ

Share this story

Posted on: Apr 17,2018

የካቲት 29/2010 ዓ.ም የሀገሪቱ የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶች እንዲመራ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማህበር መስራችና የማህበሩ የበላይ ጠባቂ አቶ ተፈራ ዋልዋ አስታወቁ፡፡ ማህበሩ ለድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞችና ከፍተኛ አመራሮች ዘርፉን አስመልክቶ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

አቶ ተፈራ በዚሁ ጊዜ ''ሀገሪቱ የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በየመስኩ እየተጠቀመች ቢሆንም ችግሩ በሙሉ አቅም አለመጠቀምና በራሳችን ዜጋ ጭንቅላትና ተቋማት መጠቀም ደረጃ ላይ አለመድረሳችን ነው'' ብለዋል፡፡ መንግስት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እስካሁንም የምርምር ተቋማት፣ የዘርፉን ባለሙያዎች ለማፍራት የሚያስችሉ ትምህርት ቤቶች ከመክፈት ባለፈ ከፍተኛ የመሳሪያ ግዥና ተከላ ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡በአሁኑ ሰዓትም በሦስተኛ ዲግሪ የተመረቁ የዘርፉ ባለሙያዎች እየተበራከቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ማህበሩም መንግስትን በዘርፉ የሚያማክሩና ናሳ ጭምር የሚሰሩ 10 አለም አቀፍ በጎ ፋቃደኛ የዘርፉ ሳይንቲስቶች ማፍራቱን ጠቁመዋል፡፡ አነዚህ ተግባራትን ጨምሮ እየተከናወኑ ያሉ ተጨማሪ ሥራዎች ሀገሪቱ ከሶስት ዓመት በኋላ በራሷ ልጆች በመሠረታዊ የዘርፉ ጉዳዮች ራሷን እንደምትችል አረጋግጠዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሀገሪቱ ለተያያዘችው የህዳሴ ጉዞ መፋጠን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልፀዋል፡፡

እንደ አቶ ተፈራ ዋልዋ ገለጻ ኢትዮጵያ የራሷን ሳተላይት ለማምጠቅ የጀመረችው ሥራ በፍጥነት እንዲሳካ ርብርቡ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን የተዛባ አስተሳሰብ ለማስተካከልና የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለተሻለ ህይወት ያለው ጠቀሜታ ለማስገንዘብ የተቀናጀ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በተለይ በየደረጃው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በስፋት ተቋቁመው አዲሱ ትውልድ የተሻለ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ቢደረግ መልካም ነው ብለዋል፡፡