የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ህንጻ ተማሪዎችን አስመረቀ

Share this story

Posted on: Apr 17,2018

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በመደበኛ የትምህርት መርሃ ግብር በኪነ-ሕንጻና በከተማ ፕላን በዲግሪ ያስተማራቸውን 34 ተማሪዎች የካቲት 10/2010 አስመረቀ።

ተመራቂዎች በቀሰሙት ዕውቀትና ክህሎት ለኪነ-ህንጻው ዘርፍና ለሀገራቸው ዕድገት ሌት ተቀን በመስራት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው የእለቱ እንግዳ የሆኑት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ኢብራሂም ዑስማን አስገንዝበዋል፡፡ በምረቃው ላይ ተገኝተው ለተመራቂዎች ዲግሪ የሰጡት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ይትባረክ ጌታቸው እንዳሉት፣ የዕለቱ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በንድፈ ሃሳብና በተግባር የተሰጠውን ትምህርት ተከታትለዋል። አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ተማሪዎችን ተቀብሎ በ10 የቅድመ ምርቃ መርሃ ግብር እያሰለጠነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ በቀጣይም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን የድሬዳዋ አስተዳደር በሰጠው 255 ሄክታር መሬት ላይ ራሱን የቻለ

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ካምፓስ ለመገንባት በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑንም ዶ/ር ይትባረክ አስታውቀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለሦስተኛ ጊዜ በኪነ- ህንፃና በከተማ ፕላን ሙያ ያስመረቃቸው ተማሪዎች ሀገሪቱ ለጀመረችው የሕዳሴ ጉዞ መሳካትና ኪነ-ህንጻው የማንነት አሻራን እንዲላበስ ለማድረግ ምሩቃኑ ብቁ መሆናቸውን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ይትባረክ ገለጻ፣ በአንደኛና በሁለተኛ ዙር የተመረቁት 65 ባለሙያዎች በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ገብተው በሀገር ዕድገት ላይ በብቃት የድርሻቸውን በመወጣት ላይ ናቸው፡፡

ዛሬ በተካሄደው የምረቃ ስነስርአት ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን ለተመራቂዎቹ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ከአስተላለፉ በኋላ ተመራቂዎቹ ሀገሪቱ ያለችበትን ወሳኝ የዕድገት ጉዞ እንዲያስቀጥሉ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎታቸውን ተጠቅመው ለሀገር  ልማት ግንባታ መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

"የተመረቃችሁበት ሙያ በዓይነቱ ልዩና ለዘመናዊ አኗኗር መሠረት የሚጥል ጥበብ ነው፤ ይህን ዕውቀት በተግባር በመተርጎም ለህዳሴው መሳካት መትጋት ይጠበቅባችኋል" በማለት ከንቲባ ኢብራሂም ተመራቂዎችን አሳስበዋል፡፡

በአጠቃላይ ውጤት 3.56 በማምጣት ልዩ ሽልማት የተሰጠው ተመራቂ ብዙነህ ሞገስ በበኩሉ በቀሰመው ዕውቀት ራሱን፣ ቤተሰቡንና ሀገሩን ለማሳደግ የበኩሉን ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡

ሌላዋ ተመራቂና ተሸላሚ ሱመያ ሙክታር የሀገር ባህላዊውን የኪነ-ህንጻ ጥበብ ከዘመናዊው ጋር በማዛመድ በዘርፉ የሚስተዋለውን ክፍተት ለማረም የተሻለ ሥራ ለመስራት ተግታ እንደምትንቀሳቀስ ተናግራለች፡፡

በ1999 ዓ.ም 754 ተማሪዎች ተቀብሎ የመማር ማስተማር ሥራውን የጀመረው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በአሁን ወቅት አምስት ኮሌጅ እና ቴክኖሎጂ እንስቲትዩት ጨምሮ በመደበኛ፣ በከረምትና በተከታታይ ትምህርት ፕሮግራሞች ከ18 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡