የህክምና ትምህርት ቤት ለ2ኛ ጊዜ የሜዲስን ተማሪዎችን አስመረቀ

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምና ት/ቤት ሚያዝያ 6/2010 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 16 ኃኪሞችን በዲግሪ አስመረቀ። ምሩቃኑ በበኩላቸው በየትኛውም ጊዜና ቦታ ህብረተሰቡን በቅንነት፣ በታማኝነትና በርህራሄ ለማገልገል ቃል ገብተዋል፡፡ በዕለቱ ለምረቃ የበቁት ሃኪሞች ላለፉት 5 ዓመት ተኩል በኮሌጁ በንድፍ ሃሳብና በተግባር የተሰጠውን ትምህርት ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው።

ዶ/ር ያሬድ ማሞ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ያሬድ ማሞ ሕክምና ከፍተኛ ማህበራዊ ኃላፊነት ያለበት ትልቅ ሙያ መሆኑን አስታውሰው፣ ምሩቃን በኮሌጁ ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ሕብረተሰቡን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ማገልገል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡" አያይዘውም ሙያው በየጊዜው ራስን ማሳደግና መማርን የሚጠይቅ ስለሆነ ሁልጊዜም ራስን በማብቃትና ለተሻለ ውጤት መስራትና መትጋት እንዳለባቸው ተመራቂዎቹን አስገንዝበዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ኢብራሂም ዑስማን በዕለቱ ለተመረቁ እጩ ሃኪሞች መንግስት በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የሕክምና ዶክትሮች እጥረት ለመፍታት እያደረጋቸው ላሉ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ይህ ምርቃት አንዱ ማሳያ ነው በለዋል፡፡ በእዚሁ መድረክ ክቡር ከንቲባው የተዘጋጀውን ሽልማት ከፍተኛ ውጤት ላመጡት ምሩቃን ሰጥተዋል፡፡

የዕለቱ ምሩቃን በበኩላቸው ህብረተሰቡን በየትኛውም ጊዜና ቦታ ያለምንም አድልኦ በቅንነት፣ በታማኝነትና በርህራሄ ቀን ከሌት ለማገልገል ቃል ገብተዋል፡፡

ከምሩቃን መካከል በትምህርቱ 3.6 በማምጣት ልዩ ተሸላሚ የሆነው ተመራቂ ዶክተር ራህመት በድሩ በበኩሉ "መነሻችንም መድረሻችንም ህብረተሰቡን በርህራሄና በቅንነት ማገልገል ነው፤ ይህን ተልዕኮ በየትኛው ጊዜና ቦታ ለመፈፀም ዝግጁ ነኝ" ብሏል፡፡

በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው ዶ/ር አለምፀሐይ ተሸመ በበኩሏ በቀጣይ በምትመደብበት ሥፍራ ሁሉ ጤናማና አምራች ሕብረተሰብ ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደምተሰራ ተናግራለች፡፡ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የዛሬዎቹን ጨምሮ በሁለት ዙር 60 ኃኪሞችን ማስመረቁ ታውቋል ፡፡